News News

Back

የመስኖ ልማት ፍላጎታቸውን በማሟላት ኑሯቸውን ማሻሻል እንዳስቻላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ:: ታህሳስ 30/2010

ባህርዳር ታህሳስ 30/2010 የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸው የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት በማሟላት ኑሯቸውን ማሻሻል እንዳስቻላቸው በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡በተያዘው የበጋ ወቅት በብሄረሰብ አስተዳደሩ እስካሁን ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ገበያ ተኮር በሆነ ሰብል ለምቷል፡፡

በባንጃ ወረዳ የአስኩና አቦ ቀበሌ አርሶ አደር ተፈራ አባዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ አራት ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡

መሬታቸውን በቡና፣ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ድንችና ስንዴ ሰብል በማልማት ከፍጆታ የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ በአንድ የምርት ወቅት እስከ 25 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የሰንከሳ ሚካኤል ቀበሌ አርሶ አደር እንዳለው አያሌው እንዳሉት በመስኖ ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት በቋሚ አትክልትና የጓሮ አትክልቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በማልማት እየተጠቀሙ ነው።

የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ቀለባቸውን ለመሸፈን ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ከመስኖ ልማት በዓመት ከ70 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመስኖ የአፕል ልማትና ችግኝ ዝግጅት ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ስድስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በፋግታ ለኩማ ወረዳ የእንደውሃ ቀበሌ አርሶ አደር መለሰ በሬ ናቸው።

ተክለው ከሚንከባከቧቸው ከ60 የአፕል ተክሎች ከሚያገኙት ምርትና ከአፕል ችግኝ ሽያጭ እስከ 50 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውም የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ከማሟላት አልፈው ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንዲመጡ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አበበ ፈንታሁን በተያዘው የበጋ ወቅት የተለያዩ የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም ከ110 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም 82 ሺህ 422 ሄክታር መሬት በቋሚ ተክሎችና ገበያ ተኮር በሆኑ ሰብሎች ማልማት ተችሏል፡፡

" በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን ቀሪ መሬት በአንደኛና ሁለተኛ ዙር በማልማት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል ባለሙያው።

በመስኖ ልማቱ ከ175 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሳው የቀረበላቸውን 123 ሺህ 382 ኩንታል ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

ባለፈው ዓመት በዞኑ በመስኖ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች በሁለት ዙር ካለሙት መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱም ተመልክቷል፡፡

ተጨማሪ ለማንበብ http://www.ena.gov.et

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.

News Archive News Archive