News News

Back

በበልግ እርሻ ከሚለማው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ47 በመቶ በላይ በዘር ተሸፍኗል

በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከሚለማው 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ47 በመቶ በላይ በዘር መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የበልግ እርሻ በአብዛኛው የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱን ክፍሎች ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ይካሄዳል።

በደቡብ ክልል የበልግ እርሻ ከክልሉ የእርሻ ምርት 50 በመቶውን ይሽፍናል፤ የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ግርማሜ ጋሩማ እንዳሉት ለበልግ የሚጠበቀው ዝናብ በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች የመጠን መቀነስ ይኖረዋል።

ይህን የዝናብ ስርጭት መሰረት ያደረገ የበልግ እርሻ ለመከወንም ክልሉ የዝናብ መጠን መቀነስ የሚገጥማቸውን አካባቢዎች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ለአርሶ አደሩ የዝናብ ስርጭት የሚያሳዩ መረጃዎችን ማድረስ፣ የሚጥለውን ዝናብ ለረጅም ጊዜ የሚያቆዩ አሰራሮችን በመከተል ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን መዝራትም ዋነኛው መፍትሄ ነው።

በሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች እየጣለ ያለው ዝናብ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የእርሻ ስራውን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ብርሃኑ እንደሚሉት፥ የዝናብ ስርጭቱ በበልግ እርሻው በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 47 በመቶውን በሰብል መሸፈን አስችሏል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በበልግ እርሻው ከ93 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ፣ ማሻ፣ ማጂና ሌሎች አካባቢዎች እየጣለ ያለው ዝናብ አርሶ አደሮቹ ከማሳ ዝግጅት ወደ ዘር እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

በአሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች የበልግ እርሻ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ያለው እንቅስቃሴም የሚያበረታታ ነው ብለዋል አቶ አለማየሁ።

የዝናብ ስርጭት መቆራረጥ በሚያጋጥማቸው የተወሰኑ አካባቢዎችም፥ ውሃን ወይም እርጥበትን የማከማቸት ስራ እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች አርሶ አደሮቹ የተሻሻሉና ፈጥኖ ደራሽ የሰብል አይነቶች እንዲዘሩ ምክረ ሃሳብ በማቅረብ፥ በአነስተኛ የውሃ ፍጆታ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ እንደ ማሾ ያሉ ሰብሎች በመዘራት ላይ ናቸው ብለዋል።

ይህም በተለያየ ምክንያት የታጣ ምርትን በማካካስ ሃገራዊ ምርትን ለማሳደግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት አጋማሽ በሚቆየው የበልግ እርሻም አርሶ አደሮች የሚጥለውን ዝናብ በመጠቀም እንደየ አካባቢዎቹ ነባራዊ ሁኔታ ከግብርናው ስራ ጋር በማስተሳሰር ሊጠቀሙ ይገባል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ለዚህም በገጠር ቀበሌ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

በሁሉም መስክ የሚከናወነው ስራ ውጤታማ እንዲሆንም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ ገብቷል።


News Archive News Archive