News News

Back

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የፈጠረችውን ምቹ ሁኔታ ኩባንያዎች ሊጠቀሙ ይገባል ተባለ::የካቲት 22/2009

 

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ራሷን ለአምራቾች ምቹ እያደረገች በመሆኑ በአፍሪካ ያሉ አምራች ኩባንያዎችም ይህንን እድል ሊጠቀሙ ይገባል ተባለ።

አምስተኛው የአፍሪካ የቢዝነስ ፎረም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የቢዝነስ ተቋማትና አምባሳደሮች በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የናይጄሪያ፣ የጀርመን፣ የሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም የኳታር አምባሳደሮችና ተወካዮችን ጨምሮ ከ100 በላይ የቢዝነስ ተቋማት ሃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የፎረሙ መስራች የሆኑት አቶ ረሺድ የሱፍ አህመድ እንደተናገሩት፥ የፎረሙ አላማ የቢዝነስ ተቋማት የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ ሀብት በመገንዘብ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር መብራህቱ መለሰ፥ የአፍሪካ ቢዝነስ ተቋማት እና አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ከአህጉሪቱ ገበያ ባሻገር ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በመረጃ የታገዘ የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ደኤታው አያይዘውም በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሀገሪቱ በርካታ የኢንደስትሪ ፓርኮችን መገንባት ችላለች ያሉት ዶክተር መብራህቱ፥ ለአብነትም በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማንሳት ማብራሪያም ሰጥተዋል።

ሀገሪቱ አሁንም በባህር ዳር፣ በድሬደዋ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ የኢንደስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ራሷን ለአምራቾች ምቹ እያደረገች በመሆኑ የአፍሪካ ባለህብቶችን በኢትዮጵያ እንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካም ሆነ የአውሮፓ ሀገራት በክፍያ አነስተኛ የሆነ ኤሌክትሪክ አለ ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ሲነሳ የነበረው ችግርም በአሁኑ ጊዜ እየተቀረፈ ነው ያለው በማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የባቡር ትራንስፖርት አማራጮችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሀይል እንዳለም ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ አያይዘውም በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በመገንባት ላይ ባሉ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ ብለዋል።

በፎረሙ ላይ በቱሪዝም፣ በግንባታ፣ በአይ.ሲ.ቲ እና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ተቋማት ሀላፊዎች ተገኝተውበታል።

Read morehttp://www.ena.gov.et


News Archive News Archive