News News

Back

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመድኃኒቶች ክትትልና ቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናት-ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር :: ሚያዝያ 30/2010

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ክትትልና ቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታወቀ።

የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲሁም የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶችና ተቆጣጣሪዎች ጋር በጋራ በመሆን  አህጉር አቀፍ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።ይህም አገራት አንድነታቸውን በማጠናከር መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች በየትኛውም አካባቢ ላይ ሲንቀሳቀሱ በትክክለኛው መንገድ የተመረቱና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለጹት፤ "በዓለም አቀፍ ደረጃ  ፈዋሽነታቸው በትክክል ያልተረጋገጡ መድኃኒቶች የሚያደርሱት ጉዳት የጤና እክል ብቻ ሳይሆን ህዝቦችን ለሞት እየዳረጉም ይገኛሉ።"

 "በተለይም ወደ አፍሪካ አገራት የሚገቡና በአፍሪካ የሚመረቱ መድኃኒቶች ችግር አለባቸው የለባቸውም የሚለውን መለየት አስቻጋሪ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው" ብለዋል።በዚህም አገሮች በጋራ በመሆን የሚመረቱ መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች የሚመረቱበት ቦታ እንዲታወቁ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና ችግር ኖሮባቸው ሲገኙም አምራቹም ሆነ አቅራቢውን ተጠያቂ ለማድረግ የሚዘረጋ አሰራር ነው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ዘርፉ ከፍተኛ ችግር የሚከሰትበት እንደመሆኑና በአንድ አገር ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ በዘርፉ ያሉ አካላትን ተሳትፎና ቅንጅት የሚጠይቅ ነው።ኢትዮጵያም ከጎረቤት አገራት ጋር ጥብቅ ትስስር በመፍጠር የክትትልና የቁጥጥር ስራውን በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፉ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ክትትልና ቁጥጥር ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሪካ ክሪሳ በበኩላቸው "አፍሪካ በጣም ጠቃሚና ትልቅ ገበያ ያላት አሀጉር ነች።""በዚህም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በጤናው ዘርፍ እያደጉ ያሉ አገራት ተሳታፊ በመሆናቸው ለታሰበው አሰራር ጠቃሚ በመሆኑ ቀጣይ ስራዎችንም ለማቅለል ጉልህ ሚና ያበረክታል" ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲሁም የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶችና ተቆጣጣሪዎች ጋር የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት እየተካሄደ ያለው ውይይት ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተካሄደው እንቅስቃሴ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃና ህጋዊ ደረሰኝ የሌላቸው የኮንትሮባንድ መድኃኒቶች ተይዘው እንዲወገዱ መደረጋቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.

News Archive News Archive