News News

Back

አፍሪካ ሙስናን መዋጋት በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አለባት- ሚስ ቢየንስ ጋዋናስ. ግንቦት 5/2010

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2010 አፍሪካ ሙስናን መዋጋት በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ልዩ አማካሪ ሚስ ቢየንስ ጋዋናስ ገለጹ።ሚስ ቢየንስ ይህን የተናገሩት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የእቅድና ኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ካካሄዱት ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደው የቀጠናው የትብብር ስርዓት ውይይት ላይ ነው።

"አፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦችን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ከፈለገች ሙስናን መከላከል በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አለባት" ሲሉ ገልጸዋል።ሙስናን መዋጋት ለአህጉሪቷ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማዳን እንደሚያስችላትም ነው የገለጹት።

አፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦችን አሳክታ ወደ ለውጥ ለመሄድ በምታደርገው ጥረት ሙስና ግልጽና ወቅታዊ ስጋት እንደሆነና ከዚህም ባለፈ ሙስና የአገልግሎት አሳጣጥ ላይ ብቻ ተጽእኖ የሚያሳድር ሳይሆን "ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣና የህግ የበላይነት እንዲሸረሸር ያድርጋል" ብለዋል።የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት በማሳጣት ለአገር አቀፍና ክልላዊ የኢኮኖሚ ልማት እንቅፋት የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል።

በሙስና ምክንያት መንግስትና ሌሎች ተቋማት የህዝብ አመኔታ ሲያጡ፣ በከባድ ትግል የተገኙ የዘላቂ ልማት ግቦች ሊባክኑ፣ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊስተጓጎሉ እንዲሁም የሰላምና መረጋጋት ችግሮች ሊገጥሙ ስለሚችሉ፤ በሚፈጠረው ፍትሐዊ ያልሆነ አሰራር "ወጣቱ እያየ ዝም ብሎ አይቀመጥም" ብለዋል።

ሙስና በዓለም አቀፍ ደረጃ  ያለውን ገጽታ ከግምት በማስገባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለው ተደራሽነት በመጠቀም በሽታ የሆነውን ሙስና ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙና በስልጣን ጊዜያቸው ሙስናን ለማጥፋት መድሐኒት ለመፈለግ በትጋት እንደሚሰሩም ተናግረዋል ሚስ ቢየንስ።በተለይም ዜጎችን አቅማቸውን በማሳደግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሙስና ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድና በማህበረሰቡ ውስጥ ሙሰኞችን  ለማስወገድ ብዙ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

በአብዛኛው እንደሚታየው "ትናንሽ አሳዎች" ብቻ እየታሰሩ መንግስትና ተቋማትን "በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሚወስዱ ሰዎች ነጻ እንዲወጡ ይደረጋል፤ ይህ ደግሞ አግባብ አይደልም" ሲሉም ገልጸዋል።በከፍተኛ ደረጃ የሚነሱ የሙስና ጉዳዮችን ለመመልከት ከሚመጣው ጫና ራሱን መከላከል እንዲችል የህግ ተርጎሚ ተቋማቶችን አሰራርና አቅም ማጠናከር  እንደሚያስፈልግና መንግስታት ሙስናን የሚታገሉ ሰዎችን መሸለምና ሙስናን የሚያጋልጡ አካለትን ጥበቃ ሊያደርግላቸውም ይገባል ብለዋል።

ሚስ ቢየንስ በግል ህይወታቸው ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍንና ሁሉም ዜጎች እኩል የእድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትግል ሲያደርጉ እንደቆዩና ሙስና አፍሪካ እያሳካች ያለችው ስራዎች ላይ የተጋረጠ በሽታ እንደሆነ እንደሚያውቁም ተናግረዋል።ሁላችንም የዚህን በሽታ መድሐኒትና መፍትሔ ለመፈለግ በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው ሚስ ቢየንስ ያብራሩት።

የአፍሪካ ህብረት "ሙስናን ተዋግቶ በማሸነፍ የአህጉሪቷን ለውጥ በዘላቂነት ማስቀጠል" በሚል የዘንድሮውን ዓመት በዚህ መሪ ቃል በመሰየሙ ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።የሙስናን አስከፊነት ካስወገድን አፍሪካን እኩልነት የሰፈነባትና ሁሉንም በጋራ በማስተሳሰርና የምንፈልጋትን አፍሪካን በመፍጠር የተቀመጡትን የ2030 እና የ2063 አጀንዳዎችን መሳካት እንደሚቻል አክለዋል።

የቀጠናው የትብብር ስርዓት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህብረቱን መርዳት በሚችልበት ሁኔታ ላይ አሻሽሎ ያወጣው የድርጊት መርሃ ግብር መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

 

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.

News Archive News Archive