News News

Back

ኦዴግ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወሰነ:: ግንቦት 6/2010

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) በሚል ስያሜ ራሱን በመጥራት የሚንቀሳቀሰው ግንባር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ገለጸ፡፡

መንግስትና ፖለቲካዊ አሰላለፉን ከኦነግ የለየው ኦዴግ ባካሄዱት ውይይትና ድርድር ድርጅቱ ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ አክብሮ ፣ ህገ-መንግስቱን በማክበር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል፡፡

ግንባሩ ፖለቲካዊ አሰላለፉን ከኦነግ በመለየት በያዘው አቋም በመንግስት በኩል ከፍተኛ አድናቆት ጋር ተቀባይነት ማግኘቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አውስቷል፡፡

አጠቃላይ ውይይቱ የተሳካና ጥሩ አገራዊ መንፈስና መግባባትም የሰፈነበት ነበር ብሏል፡፡

ይህንን በሰከነና አገር እና ህዝብን ባስቀደመ አኳኋን የሚደረግን ውይይት እና ድርድር በመንግስት ዘንድ ተቀባይነት አለው ይላል መግለጫው።

መንግስት "የአገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ ሰላማዊ በሆነ መስመር መታገልም ውጤታማ ያደርገናል" ብለው ከሚያምኑ አካላት ጋር በቀጣይም ውይይትና ድርድር ለማድረግ በጽኑ ይፈልጋል- ለተግባራዊነቱም አበክሮ ይሰራል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ሀሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል

ራሱን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ብሎ ከሰየመው ግንባር ጋር ስለ ተካሄደው ውይይትና ድርድር ከመንግስት የተሰጠ መግለጫ፡፡ይህች ሀገር የሁሉም ኢትዮጰየዊ የጋራ ቤት ናት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊም ይህችን ምትክ የሌላት ቤቱን ሰላሟን የመጠበቅ፣ ለብልጽግናዋ የመትጋት፣ ወደፊት ያራምዳታል ብሎ ያሰበውን አመለካከትም በግሉ እና በቡድን በመሆን የማራመድና ተከታዮችንም የማፍራት ህገመንግስታዊ እና እንደዜጋም ያለገደብ የሚጠቀምበት ሙሉ መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ ለሀገር እና ለወገን የሚበጅ ተግባር የምንጠብቀውን እና የምንናፍቀውን መልካም ውጤት ሊያስገኝልን የሚችለው በህግ እና በስርዓት ማእቀፍ ውስጥ ሲከናወን ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስትም የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም የአገራችንን ህገ-መንግስት ተቀብለውና በህጋዊ የመጫወቻ ሜዳ ላይ ሆነው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አቋማቸውን ማራመድ ከሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በየጊዜው ሲያሳውቅ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም መንግስት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሰረት ምንም እንኳን ከዚህ በፊት የተካሄዱት መሰል ውይይቶችና ድርድሮች ፍሬያማ ያልነበሩ ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ፖለቲካዊ አሰላለፉን ከኦነግ ከለየውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) በሚል ስያሜ ራሱን በመጥራት ከሚንቀሳቀሰው ግንባር ጋር ባካሄዱት ውይይትና ድርድር ድርጅቱ ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ አክብሮ፣ ህገ-መንግስቱን በማክበር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል፡፡ ይህ የግንባሩ አቋም በመንግስት በኩል ከከፍተኛ አድናቆት ጋር ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አጠቃላይ ውይይቱ የተሳካ፣ ጥሩ አገራዊ መንፈስና መግባባትም የሰፈነበት ነበር፡፡ ይህንን በሰከነ፣ ሀገር እና ህዝብን ባስቀደመ እና በሰለጠነ መንገድ የሚደረግን ውይይት እና ድርድር መንግስት የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል፤ ሰላማዊ በሆነ መስመር መታገልም ውጤታማ ያደርጋል ብለው ከሚያምኑ አካላት ጋር በቀጣይም ውይይትና ድርድር ለማድረግ በጽኑ ይፈልጋል- ለተግባራዊነቱም አበክሮ ይሰራል፡፡

የኦዴግ ከፍተኛ አመራሮችም በቅርብ ቀናት አዲስ አበባ እንዲገቡም ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ቀሪዎቹ ውይይቶችም እዚሁ አዲስ አበባ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ ለወደፊቱም ህገመንግስቱን ባከበረ አና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሀገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ከሚፈልጉ አካላት ጋር  ለመወያየት እና ለመደራደር መንግስት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

 

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.

News Archive News Archive