News News

መንግስት አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት አበክሮ ይሰራል - ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ :: ሚያዝያ 7/2010

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2010 መንግስት አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት አበክሮ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስታቸው በትኩረት እንደሚሰራም አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማምሻውን ከመላ አገሪቷ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረጉት ውይይት ነው መንግስት አገራዊ አንድነቱን ለማጎልበትና ለማጠናከር አበክሮ እንደሚሰራ የገለጹት።የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ፣ ውጤታማ ያልሆነና የተንዛዛ ስብሰባን ለማስቀረትና ተጠያቂነት ለማስፈን እንደሚሰሩም ተናግረዋል።በአገሪቷ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋትና ሁከት የተጎዳው ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራና የውጭ ምንዛሬ እጥረቱንም በአገር በቀል ምርቶች በመተካት ለማስተካከል እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍና እንከን የለሽ ለማድረግ እንደሚሰራ፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሆኑትን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የፍትህ አካላት በአገር ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።የአገሪቷን የትምህርት ጥራት ለማሻሻልና አካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት በትጋት አንደሚሰራም አክለዋል።በዲፕሎማሲው መስክ ከሁሉም አገራት ጋር መርህን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንደሚኖር፤ በተለይ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

የተደረገውን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አስመልክቶ ደስታቸውን የገለጹት የውይይቱ ታዳሚዎች በበኩላቸው በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት እንደሚቆሙና ለአገር ግንባታው እንቅስቃሴም በጋራ እንደሚሰለፉ እጅ ለእጅ በመያያዝ ቃል ገብተዋል። 

ምንጭ ፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.

News Archive News Archive