ወደ ሕገ መንግስት ዋና ገፅ
ምዕራፍ ስምንት : የሕግ አስፈጻሚ አካል
አንቀጽ 72 ስለ አስፈጻሚነት ሥልጣን
-
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡
-
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
-
በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሌላ አኳኊን ካልተወሰነ በስተቀር የጠቅላይሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ነው፡፡
አንቀጽ 73 የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየም
-
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል፡፡
-
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ያገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች የመንግሥት ሥልጣን ይረከባል/ይረከባሉ፡፡
አንቀጽ 74 የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር
-
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡
-
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያጸድቃል፡፡
-
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጐች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፡፡
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ይወክላል፡፡
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ይከተተላል፡፡
-
የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ በበላይነት ያስፈጽማል፡፡
-
ኮሚሽነሮችን፣ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንትን እና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያጸድቃል፡፡
-
የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብኝት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
-
በዚሀ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 7 ከተዘረዘሩት ውጭ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሲቪል ሹመቶችን ይሰጣል፡፡
-
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ ወይም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ለኘሬዚዳንቱ አቅርቦ ያሰጣል፡፡
-
ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግሥት ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት እቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖረት ያቀርባል፡፡
-
በዚህ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጐች የተሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡
-
ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፤ የስከበራል፡፡
አንቀጽ 75 ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
-
ምክትል ጠቅላይሚኒስትሩ፣
ሀ/ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፤
ለ/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶት ይሰራል፡፡
-
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 76 የሚኒስትሮች ምክር ቤት
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ሚኒስትሮችና በሕግ በሚወሰን መሰረት ሌሎች አባሎች የሚገኙበት ምክር ቤት ነው፡፡
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነው፡፡
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሚወስነው ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ነው፡፡
አንቀጽ 77 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር
-
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡ ሕጐችና የተሰጡ ውሳኔዎች በሥራ መተርጐማቸውን ያረጋግጣል፣ መመሪያዎችን ይሰጣል፡፡
-
የሚኒስትሮችንና በቀጥታ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ ሌሎች የመንግሥት አካላትን አደረጃጀት ይወስናል፣ ሥራቸውን ያስተባብራል፣ ይመራል፡፡
-
የፌዴራሉን መንግሥት ዓመታዊ በጀት ያዘጋጃል፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ያረጋግጣል፡፡
-
የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል፣ ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል፣ ገንዘብ ያትማል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ይበደራል፣ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል፡፡
-
የፈጠራና የኪነ ጥበብ መብቶችን ያስጠብቃል፡፡
-
የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ይነድፋል፣ ያስፈጽማል፡፡
-
አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
-
የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያወጣል፣ የስፈጽማል፡፡
-
ሕግና ሥርዓት መከበሩን ያረጋግጣል፡፡
-
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፣ በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው የጊዜ ወሰን ውስጥ፣ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድኝል፡፡
-
የጦርነት ጉዳዮችን ጨምሮ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡
-
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡
-
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ደንቦችን ያወጣል፡፡