ወደ ሕገ መንግስት ዋና ገፅ
ምዕራፍ ስድስት ክፍል ሁለት : የፌዴሬሽን ምክር ቤት
አንቀጽ 61 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት
-
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው፡፡
-
እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፤በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል፡፡
-
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ፤ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲወከሉ ያደርጋሉ፡፡
አንቀጽ 62 የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር
-
ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን የመተርጐም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
-
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን ያደራጃል፡፡
-
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠን መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይወሰናል፡፡
-
በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የሕዝቦች እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደርጋል፡፡
-
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ የተሰጡትን ሥልጣኖች ያከናውናል፡፡
-
በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል፡፡
-
የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጐማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወስናል፡፡
-
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፡፡
-
ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
-
የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያቋቁማል፡፡
-
ምክር ቤቱ የራሱን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ ይመርጣል፤ የራሱን የሥራ አፈጻጸምና የውስጥ አስተዳደር ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 63 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መብት
-
ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል በማናቸውም የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በሚሰጠው አስተያየት ወይም ድምጽ ምክንያት አይከሰስም፤ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡
-
ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያይዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
አንቀጽ 64 ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች
-
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባኤ የሚኖረው ከአባላቱ ሁለት ሦስተኛው የተገኙ እንደሆነ ነው፡፡ ማናቸውም ውሳኔ የሚያልፈው ስብሰባ ላይ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ድምጽ ሲደገፍ ብቻ ነው፡፡
-
አባላት ድምጽ መስጠት የሚችሉት በአካል ሲገኙ ብቻ ነው፡፡
አንቀጽ 65 ስለ በጀት
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጀቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያስወስናል፡፡
አንቀጽ 66 የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ሥልጣን
-
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል፡፡
-
ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፡፡
-
ምክር ቤቱ በአባሎቹ ላይ የወሰነውን የዲስኘሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡
አንቀጽ 67 ስብሰባና የሥራ ዘመን
-
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡
-
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 68 በሁለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን የማይቻል ስለመሆኑ
ማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ሊሆን አይችልም፡፡