ወደ ሕገ መንግስት ዋና ገጽ
ምዕራፍ አንድ : ጠቅላላ ድንጋጌዎች
አንቀጽ 1: የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ
ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡
አንቀጽ 2: የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን
የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነው ነው፡፡
አንቀጽ 3: የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ
-
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖበመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡
-
ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡
-
የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ 4: የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 5: ስለ ቋንቋ
-
ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራቸዋል፡፡
-
አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፡፡
-
የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ 6: ስለ ዜግነት
-
ወላጆቹ/ወላጆኟ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆኟ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት፡፡
-
የውጭ ሀገር ዜጐች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
-
ዜግነትን በሚመለከት ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 7: የፆታ አገላለጽ
በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡