ወደ ሕገ መንግስት ዋና ገፅ
ምዕራፍ አምስት : የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል
አንቀጽ 50 ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር
-
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
-
የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡
-
የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው፡፡
-
ክልሎች፤ በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙአቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ፡፡ ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቅተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
-
የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ስር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ ያጸድኝል፣ ያሻሽላል፡፡
-
የክልል መስተዳድር የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡
-
የክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
-
የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፡ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት፡፡
-
የፌዴራል መንግሥት በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች እንደአስፈላጊነቱ ለክልሎች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 51 የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር
-
ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፤ ይከላከላል፡፡
-
የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
-
የጤና፣ የትምህርት፣ የባሕልና ታሪካዊ ቅርስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ መመዘኛዎችና መሰረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
-
የሀገሪቱን የፋይናንስ፣ የገንዘብ፣ የውጭ ኢንቨሰትመንት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
-
የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፡፡
-
የሀገርና የሕዝብ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፡፡
-
ብሔራዊ ባንክን የስተዳድራል፤ ገንዘብ ያትማል፤ ይበደራል፤ የውጭ ምንዛሪና ገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል፡፡ ክልሎች ከውስጥ ምንጮች ስለሚበደሩበት ሁኔታ ሕግና መመሪያ ያወጣል፡፡
-
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ይወስናል፤ ፖሊሲውንም ያስፈጽማል፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ይዋዋላል፤ ያጸድቃል፡፡
-
የአየር፣ የባቡር፣ የባሕር መጓጓዣ፤ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እንደዚሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን ያስፋፋል፤ ያስተዳድራል፤ ይቆጣጠራል፡፡
-
ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጡት የገቢ ምንጮች ክልል ግብርና ቀረጥ ይጥላል፤ያስተዳድራል፤ የፌዴራል መንግሥት በጀት ያረቃል፤ ያጸድቃል፤ ያስተዳድራል፡፡
-
ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ክልሎችን የሚያስተሳስሩ ወይም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችና ሀይቆችን አጠቃቀም ይወስናል፤ ያስተዳድራል፡፡
-
በክልሎች መካከል የሚደረግን የንግድ ግንኙነትና የውጭ ንግድን ይመራል፤ይቆጣጠራል፡፡
-
በፌዴራል መንግሥት ገንዘብ የተቋቋሙ አንድ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚሸፍኑ የአገልግሎት ተቋሞችን ያስተዳድራል፤ ያስፋፋል፡፡
-
ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፡፡
-
በዚህ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጐች ያወጣል፡፡
-
በሀገሪቱ በአጠኝላይም ሆነ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ አዋጁን ያነሳል፡፡
-
የዜግነት ጥያቄ ይወስናል፡፡
-
የኢምግሬሽንና የስፖርት፤ ወደ ሀገር የመግቢያና፤ የመውጫ ጉዳዮችን፤ ስለስደተኞችና ስለ ፖለቲካ ጥገኝነት ይወስናል፤ ይመራል፡፡
-
የፈጠራና የድርሰት መብቶችን ይፈቅዳል፤ ይጠብቃል፡፡
-
አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
-
የጦር መሳሪያ ስለመያዝ የጦር መሣሪያ ሕግ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 52 የክልል ሥልጣንና ተግባር
-
በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል፡፡
-
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልሎች ሥልጣንና ተግባር የሚከተሉትን ያጠቃልላል፤
ሀ/ ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር ያዋቅራል፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፤ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፤ ይከላከላል፤
ለ/ የክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጐችን ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
ሐ/ የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
መ/ የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሰረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፤
ሠ/ ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፤ ይሰበስባል፤ የክልሉን በጀት ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
ረ/ የክልሉን መስተዳድር ሠራተኞች አስተዳደር የሥራ ሁኔታዎች በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤ ሆኖም ለአንድ የሥራ መደብ የሚያስፈልጉ የትምህርት የሥልጠናና የልምድ መመዘኛዎች ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መመዘኛዎች ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
ሰ/ የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል፡፡