ኢትዮጵያ 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪ.ሜ የሚሆን የቆዳ ስፋት ያላት ሀገር ስትሆን በአሁኑ ወቅትም ወደ 79 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት፡፡ ከዚህም ውስጥ ወደ 84 ከመቶ የሚጠጋው በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሲኖር የተቀረው በከተማና ከፊል ከተማ በሆኑ ቦታዎች ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት አወቃቀር ሲኖራት በ9 የብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም በሁለት የከተማ መስተዳድሮች የተዋቀረች ነች፡፡ አወቃቀራቸውም በሕገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት «በህዝብ አሰፋፈር፤ ቋንቋ፤ ማንነት እና ፈቃድ ላይ» ተመስርቶ ሲሆን ክልሎቹም :- የትግራይ፣ የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የጋምቤላ እና የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ሲሆኑ በተጨማሪም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደሮች ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት አንዲሁም ሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች በ800 ወረዳዎቸና ወደ 15000 በሚጠጉ ቀበሌዎች(5000 የከተማና 10000 የገጠር) የተከፋፈሉ ናቸው፡፡