የቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል የቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል

Flag of Benishangul - Gumuz Regional Stateየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከተመሠረቱ ዘጠኝ ክልሎች አንዱ ነው። የክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ ስትሆን ከአዲስ አበባ ምዕራብ አቅጣጫ 670 (ስድስት መቶ ሰባ) ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ክልሉ በስተ ሰሜን ምሥራቅ የአማራ፣ በስተ ምሥራቅ የኦሮሚያ፣ በስተ ደቡብ የጋምቤላ ክልሎች የሚያዋስኑት ሲሆን፤ በስተምዕራብ በኩል ደግሞ ከደቡብ ሱዳን እና ከሪፐብሊክ ሱዳን ጋር ይዋሠናል። የክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 50¸380 (ሃምሳ ሺህ ሦስት መቶ ሰማኒያ) ስኩየር ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ደጋ፣ ቆላ እና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባላቸው ሦስት ዞኖች፣ 19 (አሥራ ዘጠኝ) ወረዳዎች፣ አንድ ልዩ ወረዳ እና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ነው።

በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ መረጃ መሠረት የክልሉ ሕዝብ ብዛት ከ784,345 (ሰባት መቶ ሰማኒያ አራት ሺህ ሦስት መቶ አርባ አምስት) ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 385,690 (ሦስት መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና) ወይም 49.2 (አርባ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት) በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ያመላክታል። በ2008 ዓ.ም የክልሉ ሕዝብ ብዛት ወደ አንድ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 93.22 (ዘጠና ሦስት ነጥብ ሁለት) በመቶ የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር የሚኖር እና ኑሮው በግብርና ላይ የተመሠረተ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በከብት እርባታ እና በባህላዊ ወርቅ ማውጣት ተግባር ተሰማርተው ኑሮአቸውን የሚመሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም በርካታ ናቸዉ። የክልሉ ነባር ብሔረሰቦች ተብለው ከሚታወቁት አምስት ብሔረሰቦች ( በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ) በተጨማሪም የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአገው፣ የትግሬ፣ የሃድያ እና የሌሎች ብሔረሰቦች በብዛት ይገኙበታል። የብሔር፣ ብሔረሰቦቹ ቋንቋዎች በስፋት የሚነገሩ ሲሆን፤ አማርኛ ቋንቋ የክልሉ የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አባላት ቁጥር 99 (ዘጠና ዘጠኝ) ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 19ኙ (አሥራ ዘጠኙ) ሴቶች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ 80 (ሰማኒያ) የሚሆኑ ደግሞ ወንዶች ናቸው። ለበጀት ዓመቱ የተመደበው በጀት 2,936,813,543 (ሁለት ቢሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ስምንት መቶ አሥራ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አርባ ሦስት) ብር ነው። 

ክልሉ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ለምነቱ የተጠበቀ ሰፊ መሬት ባለቤት በመሆኑ ማንኛውም ዓይነት የሰብል፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት ምርቶች በማምረት ይታወቃል።በማዕድን ዘርፍም እምቅ ሀብት ያለው ሲሆን፤ የወርቅ እና የእምነ-በረድ ማዕድን በዋናነት ይጠቀሳል። በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የማይገኘው የሰማያዊ እምነ-በረድ ማዕድን ባለቤት ነው።

ተፈጥሯዊ መስህቦች
ክልሉ ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉ በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሀብቶች ባለቤት ነው። ከነዚህም መካከል፡-

  • ከተፈጥሮ ደን እና እጽዋቶች (የቀርቀሃ ደን፣ የማንጎ ተክል ደን፣ የሙጫ እና የእጣን ደኖች) ይጠቀሳሉ።
  • በመስህብነት ከሚያገለግሉ የተፈጥሮ ወንዞች (የአባይ፣ የዳቡስ፣ አባት በለስ፣ አሊ ወንዝ እና ዴዴሳ ወንዞች) ከዙሪያቸው ጥቅጥቅ ደኖች ጋር የሚያማልሉ ናቸው።
  • ተፈጥሯዊ የሆኑ የፍል ውኃ ምንጮች በስፋት የሚገኙ ሲሆን፤ የቱሪስት መስህብ በመሆን በተለይ በሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ይዘወተራሉ።
  • ታሪካዊ እና ሰው ሠራሽ መስህቦች

ታሪካዊ እና ሰው ሠራሽ መስህቦች
በክልሉ የሚገኙ ሰው ሠራሽ እና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች በርካታ ሲሆኑ፤ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የአምልኮ ቦታዎች፣ የትክል ድንጋዮች እና ቋሚ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቤተ-መንግሥት እና አስተዳደራዊ ቦታዎች፣ጥንታዊ የአርኪኦሎጂ ጥናት እና ምርምር ሥፍራዎች (ቤል ቀርቀሙ
ዋሻ አሶሳ፣ ቤል-ቤምቤሸ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ (Rock painting) እና የተለያዩ ባህላዊ መስህቦች ይገኙበታል። ከነዚህም በተጨማሪ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባቱን ተከትሎ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ እና የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።