የሀረሪ ሕዝብ ክልል የሀረሪ ሕዝብ ክልል

Flag of The Harari People's National Regional Stateየሐረሪ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

የሐረሪ ክልል ከአዲስ አበባ በ526 (አምስት መቶ ሃያ ስድስት) ኪሎ ሜትር ርቀት በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል ላይ ትገኛለች። መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ በሰሜን ንፍቀ ክበብ በ 9, 11’ እና 9 24’ ዲግሪ ላቲትዩድ መስመሮች እና በምሥራቅ ንፍቀ ክበብ በ42, 03’ እና 42 16’ ዲግሪ ሎንግትዩድ መስመሮች ላይ ትገኛለች። የአየር ንብረት ሽፋኗም 90 በመቶ ወይናደጋ እና 10 በመቶ ቆላማ እንደሆነች ጥናቶች ያመላክታሉ።የዕለቱ የሙቀት መጠን በአማካይ 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲደርስ ዓመታዊ አማካይ የዝናብ መጠን ከ700-800 ሚሊሜትር እንደሚሆን ይገመታል።

ተራራማ ገፀ-ምድራዊ አቀማመጥ ያላት ሐረር የቆዳ ስፋቷ 343,2 ኪ.ሜ(ሦስት መቶ አርባ ሶስት ነጥብ ሁለት ) ስኩዬር ኪሎ ሜትር ነው። ከባህር ወለል በላይ ያለው ከፍታ ከ1‚300-2‚200 ሜትር ሲደርስ ከፍተኛው ስፍራ አውሐኪም ተራራ ሲሆን2‚200 ሜትር ከፍታ አለው። ዝቅተኛው ስፍራ የኤረር ሸለቆ ሲሆን 1300 ሜትር ከፍታ አለው።

በክልሉ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችየሚኖሩ ሲሆን፤ በ1999 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት የክልሉ ሕዝብ ብዛት 232‚000(ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ) እንደሆነ ያመለክታል። ከነዚህም ውስጥ 129,224 (አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ ሃያ
አራት) የሚሆነው ሕዝብ በከተማ ሲኖር 102,776 (አንድ መቶ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሰባ ስድስት) ደግሞ በገጠር ይኖራል።

ሐረሪ ክልልን በሰሜን የኮምቦልቻ፣ በሰሜናዊ ምሥራቅ ጃርሶ፣ በደቡብ የፈዲስ፣በምዕራብ የሀረማያ እና በምሥራቅ የጉርሱም እና የባቢሌ ወረዳዎች ያዋስኗታል።

የክልሉ የሥራ ቋንቋ የሐረሪ ቋንቋ እና ኦሮምኛቋንቋ ሲሆን፤ አማርኛ፣ኦሮምኛ፣ ጉራግኛ እና ሱማልኛቋንቋ ተናጋሪዎችምይገኙበታል።የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት 36 (ሰላሳ ስድስት) አባላት ያሉት ሲሆን፤ በሁለት ጉባኤዎች ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ጉባኤ እና የሐረሪ ጉባኤ ናቸው።

የቱሪስት መስቦች
 

የጀጎል ግንብ እና አምስት በሮች

በዓለም አቀፍ ቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የጀጎል ግንብ ሐረርን ከ1551-1559 ያስተዳደሩ በ42ተኛው አሚር ኑር ቢኒ ሙጃሂድ ዘመን የተገነባ ነው። ጀጎል 66 ሔክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ የግንቡ ከፍታም 12 ጫማ ነው። የጀጎል ግንብ አምስት ለመግቢያ እና መውጫ ሚያገለግሉ በሮች አሉት። እነሱም ሱቅጣጥ በሪ፣ አርጎ በሪ፣ አሱም በሪ፣ አስዲን በሪ እና በድሮ በሪ ይባላሉ። እነኚህ በሮች ከሐረሪኛ ስማቸው በተጨማሪ የአረብኛ፣ የአማርኛ እና የኦሮምኛ ስሞችም አሏቸው። ጀጎል ውስጥ 359 (ሦስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) የሚሆኑ ቀጫጭን መንገዶች አሉ።  ከነዚህም ውስጥ መገራዋ ዊጌር (አስታራቂ መንገድ) የሚባለው መንገድ ጠባብ በመሆኑ ከአንድ ሰው በላይ አያሳልፍም።

Pages: 1  2