ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ትቀጥላለች - የተመድ ሪፖርት:: ጥር 8/2010

አዲስ አበባ ጥር 8/2010 ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን እንደምትቀጥል የተመድ ሪፖርት አመለከተ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2018 ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታና ትንበያ ሪፖርት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።

በሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ቀዳሚ አገሮች መካከል ሆና ትቀጥላለች።በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በቢዝነስ በኩል የሚያሰሩ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው ለዕድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ሪፖርቱ ያሳያል።

በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪና በውጭ ኢንቨስትመንት የሚደረገው የፋይናንስ ማበረታቻ እንዲሁም በቱሪዝም መስክ ከፍተኛ የአገር ውስጥ ፍላጎት እየጨመረ መምጣት ዕድገቱን እየደገፈ እንደሚቀጥልም ነው የተነበየው።በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት አገሪቱ ወደ ውጭ በምትልካቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ዋጋ መቀነስና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ቢያጋጥምም ኢኮኖሚዋ ጠንካራ የመቋቋምና የማገገም ሁኔታ አሳይቷል።

ጠንካራ የግል ፍጆታና የኢንቨስትመንት መጨመር እንዲሁም መንግስት በመንገድ፣ በኃይልና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መሰረተ ልማቶች የሚያውለው በጀት ማደግ ትልቅ ሚና መጫወቱንም ሪፖርቱ አስቀምጧል።የሰርቪስ ሴክተሩ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀዳሚ ቢሆንም ድርሻው እየቀነሰ የኢንዱስትሪ ሴክተሩ እየተስፋፋ መሆኑንም ሪፖርቱ ያሳያል።

በሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ጂ.ዲ.ፒዋ 2 ነጥብ 5 በመቶ የበጀት ጉድለት አስመዝግባለች።
አገሪቱ የብር የመግዣ ዋጋ ብትቀንስም የዓለም አቀፍ የዕቃዎች ገበያ ደካማ በመሆኑ የውጭ ንግዷ የተረጋጋ ሆኖ እንደሚቀጥል ሪፖርቱ ይተነብያል።የአገሪቱ የዋጋ ግሽበትም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአንድ አሃዝ እንደሚቀጥል አመላክቷል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት 3 በመቶ ያደገው የአፍሪካ ጂዲፒ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በቅደም ተከተል 3 ነጥብ 5 እና 3 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ያሳያል ይላል ሪፖርቱ።ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ምስራቅ አፍሪካ በ5 ነጥብ 3 በመቶ ከአፍሪካ ፈጣን የጂዲፒ ዕድገት ማስመዝገቡን ሪፖርቱ ያሳያል።

ለዚህም የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንትና የአካባቢያዊ ገበያ ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ያሳያል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ምስራቅና ደቡብ ኤዥያ እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካ ከ5 በመቶ በላይ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገባቸውን እንደሚቀጥሉም ሪፖርቱ አመላክቷል።

የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትም በማገገም በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ሶስት በመቶ ማደጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርት አመልክቷል።ይሄ እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ ከፍተኛው ዕድገት ሲሆን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።

የተሻሻለው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታ አገሮች ሥራ አጥነትን በመቀነስ፣ የኢኮኖሚ ልዩነትን በማጥበብና ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት የሆኑና ስር የሰደዱ ችግሮችን በማቃለል ላይ እንዲያተኩሩ ዕድል መፍጠሩን ሪፖርቱ አብራርቷል።ታዳጊ አገሮች የተቋማት አለመጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ዕጥረት፣ የተፈጥሮ ውድመትና የፀጥታና ፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮችን እየተጋፈጡ እንደሚቀጥሉም አመልክቷል።

ከዚህ የተነሳ በጣም ጥቂት አገሮች የዘላቂ ልማት ግብና የምጣኔ ሀብት ዕድገታቸውን 7 በመቶ እንደሚያደርሱ ሪፖርቱ ተንብዮዋል።
ከ2016 ጋር ሲነፃፀር ሁለት ሶስተኛው የዓለም አገሮች በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2017 ጠንካራ ዕድገት ማሳየታቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

ተጨማሪ ለማንበብ www.ena.gov.et