የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል

Flag of SNNP Regional Stateየደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግሥት በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል-በላቲትዩድ መስመር በ4027” እና በ 8030” ሰሜን መካከል፤ በሎንግዩቲዩድ መስመር በ340 21, ምሥራቅ እና በ390 10’ ምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል። ክልሉ በሰሜን ምሥራቅ እና በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከኦሮሚያ፣ በምዕራብ ከጋምቤላ ክልል እንዲሁም በደቡብ ኬንያ፣ በደቡብ ምዕራብ ደግሞ ከሱዳን ጋር ይዋሰናል።

የክልሉ የቆዳ ስፋት 110,932 (አንድ መቶ አሥር ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ሁለት) ስኩዬር ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት አሥር በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። ከዚህ ውስጥ 48.9 (አርባ ሥምንት ነጥብ ዘጠኝ) በመቶ ቆላማ፣ 8.4 (ሥምንት ነጥብ አራት) በመቶ ደጋ፣ 33.9 (ሰላሳ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ) በመቶ ወይናደጋ፣ 8.4 (ሥምንት ነጥብ አራት) ሐሩር እና ቀሪው 0.2 (ዜሮ ነጥብ ሁለት) በመቶ ውርጫማ የአየር ንብረት ያለው ነው። ከክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት
ውስጥ 26 (ሃያ ስድስት) በመቶው የለማ፣ 22 (ሃያ ሁለት) በመቶው ሊለማ የሚችል፣12 (አሥራ ሁለት) በመቶው የግጦሽ፣19 (አሥራ ዘጠኝ) በመቶው በቁጥቋጦ እና 12 (አሥራ ሁለት) በመቶ በደን ሲሸፈን ቀሪው 10 (አሥር) በመቶ የሚሆነው ድንጋያማ፣ አለታማ እና ረግረጋማ መሬት
ነው። አማካይ የዝናብ መጠኑም ከ400-2‚200 (አራት እስከ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ) ሚሊ ሊትር ይደርሳል።

በፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የስታስቲክስ እና የሥነ-ሕዝብ መረጃ መሠረት የክልሉ ሕዝብ ቁጥር 18.93 (አሥራ ሥምንት ነጥብ ዘጠና ሦስት) ሚሊዮን ነው። ይህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 20 (ሃያ) በመቶ ድርሻ ሲኖረው፤ 11.5 (አሥራ አንድ ነጥብ አምስት) በመቶ በከተማ እንዲሁም 88.5 (ሰማኒያ ሥምንት ነጥብ አምስት) በመቶ በገጠር ይኖራል። በክልሉ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አሰፋፈራቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ማንነታቸውን እና ፈቃዳቸውን መሠረት በማድረግ የተቋቋሙ የየራሳቸው የዞን እና የወረዳ አስተዳደር አላቸው።

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መንግሥት መስተዳድር 3‚884 (ሦስት ሺህ ሥምንት መቶ ሰማኒያ አራት) ቀበሌዎች ያሏቸው 133 (አንድ መቶ ሰላሳ ሦስት) ወረዳዎች እና 22 (ሃያ ሁለት) የከተማ አስተዳደሮችን ያቀፉ 14 (አሥራ አራት) ዞኖች እና አራት ልዩ ወረዳዎችን ያጠቃልላል። በነዚህ አስተዳደሮች በመንግሥት ዕውቅና ያላቸው የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል እና ማኅበራዊ ልምድ ያሏቸው 56 (ሃምሳ ስድስት) ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ይገኛሉ። የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው።

ከአንድ በላይ ብሔረሰቦች በሏቸው እንደ ደቡብ ኦሞ፣ ጉራጌ እና ሰገን ሕዝቦች ዞኖች የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን፤ የሌሎቹ ዞኖች የሥራ ቋንቋ የየብሔረሰቡ ቋንቋ ነው። የክልሉ ምክር ቤት አባላት ብዛት 348 (ሦስት መቶ አርባ ሥምንት) ሲሆን፤ 67 (ስድሳ ሰባቱ) ወይም 47.9 (አርባ በሰባት ነጥብ ዘጠኝ) በመቶ ሴቶች ናቸው።

የክልሉ ልዩ መገለጫዎች

ክልሉ የራሳቸው ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግ፣ ማኅበራዊ ልማድ እና አኗኗር ያላቸው 56 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድ ላይ በፍቅር እና በመተሳሰብ ይኖራሉ። ይህ ከመጠለያ አቀላለስ ጀምሮ በአለባበስ፣ በአጨፋፈር፣ በቋንቋ ያላቸውን ልዩነት አዋህደው መኖራቸው ውህደ-ውበት እና ኅብረ-ጌጥ አድርጓቸዋል። እነዚህ ልዩነቶች በአንድ መስተዳድር ጥላ ሥር ሆነው ለጋራ ዕድገት መሥራታቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።

የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆነ የቡና ምርት በማምረትም ይታወቃል። የቡና ልማት በመጀመሪያው የትራንስፎርሜሽን ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ለምቶ ምርት የሚሰጠው 455‚000 (አራት መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ) ሔክታር ደርሷል። በ2008 በጀት ዓመት  61,178.98 (ሁለት መቶ ስድሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰባ ሥምንት ነጥብ ዘጠና ሥምንት) ቶን እሸት ቡናና 80,396.07 (ሰማኒያ ሺህ ሦስት መቶ ዘጠና ስድስት ነጥብ ዜሮ ሰባት) ቶን ጀንፈል ቡና ተሰብስቧ። እንዲሁም 46,341.64 (አርባ ስድስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ አንድ ነጥብ ስድሳ አራት) ቶን የታጠበ እና 40,350.073 (አርባ ሺህ ሦስት መቶ ሃምሳ ነጥብ ዜሮ ሰባ ሦስት) ቶን ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል።

ክልሉ ተፈጥሯዊ፣ባህላዊ እና ታሪካዊ የሆኑ ቅርሶች እና የቱሪስት መስህቦች ይታወቃል። ለዚህም የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል፣ የኮንሶ መልክዓ-ምድር፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የኦሞ- ሸለቆ አርኪዮሎጂካል ሥፍራ ይጠቀሳሉ። እነዚህም በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ ተመዝግበዋል።
የብሔረሰቡን ባህል፣ ወግ እና ማኅበራዊ ልምድ ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ማጎ፣ ማዜ፣ ጨበራ-ጩርጩራ፣ ሎካ፣ ጊቤ-ሸለቆ፣ ኦሞ-ሸለቆ እና የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርኮች በውስጣቸው ካሉት የዱር እንስሳት ጋር እንዲሁም ፏፏቴዎች እና ፍል ውኃዎች የቱሪስት መስህቦች ናቸው። በተጨማሪም ከስምጥ ሸለቆ ሐይቆች መካከል ሀዋሳ፣ አባያ እና ጫሞ ሐይቆች፣ በኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በዳውሮ፣ በሸካ፣ በቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኙት ጥብቅ ደኖች በተለያዩ አካባቢዎች ያሉት የገፀ-ምድር እና የከርሰ-ምድር ማዕድናት በክልሉ ካሉት የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ለአብነት የተጠቀሱ ናቸው። በበጀት ዓመቱ የዘርፉን የማስፈጸም ዓቅም ከመገንባት ጀምሮ በየመስኩ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ተችሏል።

የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ተግባራት

በዘርፉ ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል የሰብል ልማት ይጠቀሳል። በ2008 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ ወቅት በአዝርዕት ሰብሎች 791‚634.2 (ሰባት መቶ ዘጠና አንድ ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ አራት ነጥብ ሁለት) ሔክታር በማልማት 17,763,835 (አሥራ ሰባት ሚሊዮን ሰባት መቶ ስድሳ ሦስት ሺህ ሥምንት መቶ ሰላሳ አምስት) ኩንታል ምርት ተመርቷል። በበጀት ዓመቱ በበልግ እርሻ ወቅት በሁሉም የሰብል ዓይነቶች 92.2 (ዘጠና ሁለት ነጥብ ሁለት) በመቶ ሔክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል። የሰብል ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የምርምር ተግባራት በአገዳ እና ብዕር ሰብሎች ዝሪያ ማሻሻያ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ሰብሎች ምርታማነት ማሻሻያ እና በሰብል በሽታ ተባይ እና አረም ቁጥጥር የምርምር ተግባራት ተከናውኗል። የአሲዳማ አፈር ምርታማነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የምርምር ተግባራት በተመረጡ የአርሶ አደር ማሳዎች በገብስ እና በስንዴ ላይ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተከናውኗል።