የመንግሥት አወቃቀር የመንግሥት አወቃቀር

ምዕራፍ አራት : የመንግሥት አወቃቀር

አንቀጽ 45 ሥርዓተ መንግሥት

 • የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው፡፡


አንቀጽ 46 የፌዴራል ክልሎች

 1. የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
 2. ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው፡፡

አንቀጽ 47 የፌዴራል መንግሥት አባላት

 1. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት የሚከተሉት ናቸው፡፡
  1. የትግራይ ክልል
  2. የአፋር ክልል
  3. የአማራ ክልል
  4. የኦሮሚያ ክልል
  5. የሱማሌ ክልል
  6. የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል
  7. የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል
  8. የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል
  9. የሐረሪ ሕዝብ ክልል
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፡፡
 3. የማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት ሥራ ላይ የሚውለው፤
  ሀ/ የክልል መመስረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፤
  ለ/ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤
  ሐ/ ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ሲደገፍ፤
  መ/ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ፤
  ሠ/ በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፡፡
 4. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት እኩል መብትና ሥልጣን አላቸው፡፡

አንቀጽ 48 የአከላለል ለውጦች

 • የክልሎች ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል፡፡ የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጐት መሠረት በማድረግ ይወስናል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ አስቀጽ 1 መሰረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
አንቀጽ 49 ርዕሰ ከተማ

 1. የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡
 2. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
 3. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል፡፡
 4. የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሰረት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡
 5. የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡