የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል

ምዕራፍ አምስት የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል

አንቀጽ 50
ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር
 1. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብ ሊክ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው ፡፡
 2. የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡  
 3. የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፣ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው ፡፡
 4. ክልሎች፣ በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙአቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ፡፡ ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቅተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
 5. የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ስር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል፣ ያሻሽላል፡፡
 6. የክልል መስተዳድር የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡
 7. የክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
 8. የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፡፤ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት፡፡
 9. የፌዴራል መንግሥት በዚህ ሕገ መንግ ሥት አንቀጽ ፶1 ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች እንደአስፈላጊነቱ ለክልሎች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡

አንቀጽ 51
የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር

 1. ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፣ ይከላከላል፡፡
 2. የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራ ዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡
 3. የጤና፣ የትምህርት፣ የባሕልና ታሪካዊ  ቅርስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ መመዘኛዎችና መሰረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡
 4. የሀገሪቱን የፋይናንስ ፣ የገንዘብ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎ ችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡
 5. የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፡፡
 6. የሀገርና የሕዝብ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፣ ይመራል፡፡
 7. ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል፣ ገንዘብ ያትማል ፣ ይበደራል፣ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል ፡፡ ክልሎች ከውስጥ ምንጮች ስለሚበደሩበት ሁኔታ ሕግና መመሪያ ያወጣል፡፡
 8. የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ይወስናል፣ ፖሊሲውንም ያስፈጽማል፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ይዋዋላል፣ ያጸድቃል፡፡
 9. የአየር፣ የባቡር ፣ የባሕር መጓጓዣ፣ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እንደዚሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን ያስፋፋል፣ ያስተዳድራል፣ ይቆጣጠራል፡፡
 10. ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጡት የገቢ ምንጮች ክልል ግብርና ቀረጥ ይጥላል፣ ያስተዳድራል፣ የፌዴራል መንግሥት በጀት ያረቃል፣ ያጸድቃል፣ ያስተዳድራል፡፡
 11. ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ክልሎችን የሚያስተሳስሩ ወይም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችና ሀይቆችን አጠቃቀም ይወስናል፣ ያስተዳድራል፡፡
 12. በክልሎች መካከል የሚደረግን የንግድ ግንኙነትና የውጭ ንግድን ይመራል፣ ይቆጣጠራል፡፡ 
 13. በፌዴራል መንግሥት ገንዘብ የተቋቋሙ አንድ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚሸፍኑ የአገልግሎት ተቋሞችን ያስተዳ ድራል፣ ያስፋፋል፡፡
 14. ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፡፡
 15. በዚህ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጐች ያወጣል፡፡
 16. በሀገሪቱ በአጠቃላይም ሆነ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፣ አዋጁን ያነሳል፡፡
 17. የዜግነት ጥያቄ ይወስናል፡፡
 18. የኢምግሬሽንና የፓስፖርት፣ ወደ ሀገር የመግቢያና፣ የመውጫ ጉዳዮችን፣ ስለ ስደተኞችና ስለ ፖለቲካ ጥገኝነት ይወስናል፣ ይመራል፡፡
 19. የፈጠራና የድርሰት መብቶችን ይፈቅዳል፣ ይጠብቃል፡፡
 20. አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
 21. የጦር መሣሪያ ስለመያዝ ሕግ ያወጣል፡፡

አንቀጽ 52
የክልል ሥልጣንና ተግባር

 1. በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልሎች ሥልጣንና ተግባር የሚከተሉትን ያጠቃልላል፣
  ሀ) ራስን በራስ ማተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር ያዋቅራል፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል፤
  ለ) የክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች   ሕጐችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል፣
  ሐ) የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና እቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፣
  መ) የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሰረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፣
  ሠ)  ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፣ የክልሉን በጀት ያወጣል፣ ያስፈጽ ማል፣
  ረ) የክልሉን መስተዳድር ሠራተኞች አስተዳደር የሥራ ሁኔታዎች በተመለ ከተ ሕግ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፣ ሆኖም ለአንድ የሥራ መደብ የሚያስፈልጉ የትምህርት የሥልጠናና የልምድ መመዘኛዎች ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መመዘኛዎች ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡        
  ሰ) የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል ፣ ይመራል ፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል ፡፡