የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ4 አሰተዳደራዊ ዞኖች፣ በአንድ ልዩ ዞን፣ በ35 ወረዳዎች እና በ74 ከተማዎች የተዋቀረ ነው፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የከፍተኛ አስተዳደር አካል ሲሆን 152 የካቢኔ አባላትን የያዘ ነው፡፡ የህግ አስፈፃሚው አካል በ16 ተወካዮች የተዋቀረ ነው፡፡

ርዕሰ ከተማ

መቀሌ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ ከተማ ነች፡፡

የስፍራው አቀማመጥ

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ጫፍ የሚገኝ ሲሆን ክልሉ በሰሜን ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከአፋር ክልል፣ በደቡብ ከአማራ ክልል እንዲሁም በምእራብ ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር ይዋሰናል፡፡

የቆዳ ስፋት

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 80000 ስኩ.ኪ.ሜ የሚገመት የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡

ስነ-ህዝብ

በ1994 በተገኘው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ብዛት 3,136,267 ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1,542,165 ወንዶች እና 2,667,789 ሴቶች ናቸው፡፡ በሀይማኖት ረገድም 95.5% የኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ 4.19% የእስልምና እና 0.4% የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነው፡፡ በብሄር ስብጥር ረገድም 94.98% የትግራዊ፣ 2.6% የአማራ፣ 0.7% የኢሮብ እና 0.05% የኩናማ ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡

ትግርኛ የክልሉ የስራ ቋንቋ በመሆን ያገለግላል፡፡ 

ዋነኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች

በትግራይ ብሔራዊ ክልል ከሚገኘው ህዝብ 83% የሚሆነው በግብርና ስራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ እና ገብስ ዋነኛ የሰብል ምርቶች ሲሆኑ ባቄላ፤ የጥራጥሬ እህሎች፣ ሽንኩርት እና ድንች እንዲሁ በክልሉ ይመረታሉ፡፡ ተዳፋታማ የመሬት አቀማመጥ ባላቸው የክልሉ አካባቢዎች የመስኖ እና የእርከን መፍትሄዎችን በመጠቀም የእርሻ ስራ ይከናወንባቸዋል፡፡ የትግራይ ክልል የጥጥ፣ የእጣን፣ የሰሊጥ እና የተለያዩ ማእድናትን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡ ከክልሉም የመሬት ይዞታ 1.5 ሚሊዮን ሄክታር መልማት የሚችል ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን ሄክታሩ ለእርሻ አገልገሎት የዋለ ነው፤ የተቀረው 420,877 ሄክታር መሬት ደግሞ የእርከን ስራን በመጠቀም የለማ ነው፡፡ የተለያዩ የእደ-ጥበብ(እንደ ወርቅ ማንጠር፣ የስዕል እና የእንጨት ቅርፃ ቅርፅ) ስራዎች ሌላው በክልሉ በሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ የሚስተዋሉ የስራ አንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡

የመሬት አቀማመጥ እና የአየር ንብረት

ምንም እንኳን ክልሉ ከ3,250 - 3,500 ሜትር ከፍታ ባላቸው የተራራ ሰንሰለቶች እና የተፈጥሮ መስህቦች የተከበበ ቢሆንም፤ ለዘመናት ሲፈራረቅበት የቆየ የመሬት መሸርሸር፣ የደን መጨፍጨፍ እና ከመጠን በላይ የሆነ የግጦሽ መሬት አጠቃቀም የክልሉን መሬት ለደረቅና ዛፍ-አልባ ሜዳዎች፣ኮረብታዎችና ተራራዎች አጋልጦታል፡፡ ይህ ክልል ሁለት እጅግ በጣም የተለያዩ የከፍታ ልዩነቶችን ያስተናግዳል፡፡ የክልሉ የከፍታ መጠን ከባህር ጠለል በላይ ከ600 - 2,700 ሜትር ሲሆን የተከዜ ሸለቆ ከባህር ጠለል በላይ 550 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ "የክሳድ ጉዶ" የተራራ ጫፍ ደግሞ ከባህር ጠለል በላይ በ3,935 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በመሀከላዊ ደጋማ አካባቢዎች ከሚገኙ የትግራይ ውብ የተፈጥሮ እይታዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ የአየር ንብረት ያላችው አካባቢዎች ሲገኙ 39% ቆላማ፣ 49% ወይና ደጋማ፣ 12% ደጋማ ቦታዎች ናቸው፡፡ የክልሉ አመታዊ አማካኝ የዝናብ መጠን ከ450 – 980 ሚ.ሜ ይደርሳል፡፡

ወንዞችና ሀይቆች

ከአማራ ብሄራዊ ክልል የሚነሳው የተከዜ ወንዝ እንዲሁም ከኤርትራ የሚነሳው የመረብ ወንዝ የትግራይ ክልልን የሚያቋርጡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ናቸው፡፡ እንደ ገባ፣ ወሪ፣ በርበር፣ አርቋ እና ጠጠር የተባሉ ለመስኖ ስራ ጠቃሚ የሆኑ አነስተኛ ወንዞችም በክልሉ ይፈሳሉ፡፡ የተከዜ ወንዝ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይልን ለማመንጨት ተስፋ የተጣለበት ወንዝ ነው፡፡ ሌላው በክልሉ የሚገኘው የአሸንጌ ሀይቅ ውብ የሆኑ አእዋፋትን ለመመልከት እና አሳ ለማጥመድ የተመቸ እና ቀልብን የሚስብ የተፈጥሮ መስዕብ ነው፡፡

Pages: 1  2